ትንሽ ጠንከር ፡ በል ይኑርህ እውቀት ተጠንቅቀህ ስማን ፡ እንዳትሳሳት እኛ መላይኮች ፡ ነን አናውቅም ውሸት ተልከን ነው ፡ እንጂ እኛ አናዝበት ይሄንን ነግረውኝ ፡ ስንሰናበት ዋሪዳው መጣና ፡ ቆይ አለኝ አመት
ጌታው ሸህ ሁሴን ጅብሪል ፡ ፍርዱ እንደት እንደጀመራቸው ፡ ምን ምን እንዳጋጠማቸው ፡ ዘርዘር ባለ መንገድ አስቀምጠውታል ፣ አንድ አንዱ ነገር ተመወሳሰቡ የተነሳ ፡ ግጥሙን መከታተሉ ፡ ከማስረዳቱ ይቀላል።
ሰው ብዙ ያወራል ፡ ፈጥሮ በግምት መቼም በኒ አደም ፡ ለወሬ አይታክት ጥቂት ፍንጭ ካየ ፡ ትንሽ ምልክት ያችን ይይዝና ፡ እንደ ሽልማት አብሮ እንደነበረ ፡ ባይኖቹ እንዳያት ምንም ሳይሰማው ፡ የፍርሃት ስሜት ሰው ምን ይለኝ ሳይል ፡ ቁሞ ከሰው ፊት ውሸቱን ያወራል ፡ ሰዎች እያዩት ምን ተብሎ ይጠራል ፡ የዚህ ሰው አይነት? እኔ ልንገራችሁ ፡ ስለኔ ሂወት ልታምኑም ላታምኑም ፡ አላችሁ መብት ትንሽ ከበድ ይላል ፡ በቃል ሲያወሩት ገና ትንሽ ሁኘ ፡ በስድስት አመት ተጫወቼ ሳልጠግብ ፡ እንደ ህፃናት ገና ለሚመጣው ፡ መሰለኝ ታይቶት ግን ትንሽ ጠብቀን ፡ ሲለኝ ሰማሁት ትንሽ ጠንከር በል ፡ ይኑርህ እውቀት ተጠንቅቀህ ስማን ፡ እንዳትሳሳት እኛ መላይኮች ነን ፡ አናውቅም ውሸት ተልከን ነው እንጂ ፡ እኛ አናዝበት ይሄንን ነግረውኝ ፡ ስንሰናበት ዋሪዳው መጣና ፡ ቆይ አለኝ አመት ጫትክን እየቃቃምክ ፡ ሳትወሳለት ተዱሮ ሰዎች ጋር ፡ ተጫወት ተቤት እኔም ኸልዋ ፡ ገባሁ ቆየሁ አንድ አመት አላህ ያሳየኝን ፡ ተማምኜበት ሙእጅዛ ስጠብቅ ፡ ታላህ ምልክት መነጥር ተሰጠኝ ፡ ታላህ ግምጃ ቤት ማንም ሰው ያላያት ፡ ማንም ያልነካት አበጥራ የምታይ ፡ ሸክ የሌለባት ባህር አይጋርዳት ፡ ጎራ አይከልላት ቢደበቅ ቢሸሸግ ፡ የማያመልጣት አታረጅ አትዝግ ፡ ወይ አትማራት አላህ በጥበቡ ፡ በጁ የሰራት ለወደደው ባሪያው ፡ አዝኖ የሚሰጣት እንግዲያ እውቀት የለኝ ፡ የምኮራበት እንደቃልቶቹም ፡ የለኝም ትምህርት እድሜየም ትንሽ ነው ፡ እኔ በዛ ወቅት ለአላህ ልዩ ነገር ፡ ምን አድርጌለት፧ አዝኖልኝ ነው እንጂ ፡ ረበል ኢዘት ገና ሲወጥነኝ ፡ ሲፈጥረኝ ከጧት በጁ ስለሆነ ፡ መስጠት መቀማት ለፈለገው ቢሰጥ ፡ ማንስ ጠይቆት ሰው አይረዳውም ፡ ይሄን ሲነግሩት አንዳንዱም ከብዶት ነው ፡ አንዳንዱም ቅናት መነጥሯ እኔ ጋር ፡ አለች እስክሞት ዝም ብየ እንዳይመስልህ ፡ የምወሻክት የልጅ ልጅ ይመጣል ፡ የሚረክባት ከሞትኩኝ በኃላ ፡ ከብዙ አመታት ሰው እንዳይታለል ፡ እንዳይሳሳት ተቀኝ ጉንጩ ላይ ፡ አለው ምልክት የሆነች ነገር ናት ፡ እንደ ኪንታሮት በጣም ትንሽ ሁና ፡ ደመቅ ያለችናት መልከ መልካም ልጅ ነው ፡ ደስ የሚል ሲያዩት ቅንድቡ ግጥም ነው ፡ ያይኑ ሽፋሽፍት እራሱን ያመዋል ፡ ቀንና ሌሊት ሲቋደስ ብቻ ነው ፡ የሚበርድለት አፍንጫው ቀጥ ያለ ፡ የአረቦች አይነት ፊቱ ወለል ያለ ፡ እንደ መስታወት የቀማመሰ ነው ፡ ተዘመኑ እውቀት ማንበብ ግን ይወዳል ፡ የቁርዓን ዓያት ፍርድ እንደኔ አይፈርድም ፡ ህልሙ ግን አይስት ሰው ዝምብየ ፡ መስሎት የምቀሳፍት ፍርድ እየፈረድኩኝ ፡ ስናገር ትንቢት ግጥሙ ተጥፎልኝ ፡ ነው እያየሁት በወርቅማ ቀለም ፡ በነጭ ወረቀት ጥፌው እንዳይመስልህ ፡ ተራሴ አንደበት መስሎህ ተጠራጥረህ ፡ እንዳትሳሳት እኔ እንኳን እራሴ ፡ ባይኔ እያየሁት ማመን ያቅተኛል ፡ ጉድ አጃይበት ለቃልቾቹማ ፡ ከባድ ነው በውነት ግን አላህ ተሻልህ ፡ የለም የሚያቅት እኔ ምን ልነግርህ ፡ እራስህ ገምት መቸም ተቆጥሮ አያልቅ ፡ የጌታችን ኸይር ማጀቱ ሰፊ ነው ፡ የአላህ ሚስጥር አላህ ያሳየኝ ፡ እስቲ ልናገር ተሰጠኝ በኃላ ፡ ያንን መነጥር አለሙን አየሁት ፡ ተዳር አስተዳር አንዳትሸክከኝ ፡ እንዳትጠረጥር ውሽት እንዳይመስልህ ፡ የምልህ ነገር ንጉስ እየፈራን ፡ ሳይጠላን አሽከር ውስብስብ ነበረ ፡ ብዙ የሚያስቸግር የሚያሾፍም ነበር ፡ የሚስቅ ናኪር ዝምብየ መስሏቸው ፡ የምቀባጥር በጣም ተደፋፈርን ፡ ታንዳንዶችስ ጋር አፍ አውጥተው ፡ ዟሂር ይሰድቡኝ ጀመር እንደነሱ እስላምነኝ ፡ አይደለሁ ካፊር በእስላም ቀጥፎ ፡ ማውራት ዋሽቶ መናገር ከባድ ነው ፡ ቅጣቱ በሰማይ በምድር ይሄነን አውቃለሁ ፡ ምንም ባልማር ይሄን ህግ ፡ አልጥስም ምንም ብዳፈር ወዲያው ስሜ ፡ ታውቆ ሽዋና ሃረር እኔም በማስታውት ፡ ፊቴን ሳሳምር መደዱ ቀጠለ ፡ የጌታችን አምር ንጉሶች ፈለጉኝ ፡ ሃፍታምም ታጅር ምን ያውቅ ፡ ይሆን ተብሎ ምን ልዩ ነገር ጠንቋይ መስያቸው ፡ ስር የምቆፍር የምፈራው መስሎት ፡ የማወራ አሽሙር አፄ ቴዎድሮስን ፡ አግኝቸው ነበር አንድ የሚያሳስበው ፡ ነበረው ሚስጥር ተንግሊዞቹ ጋር ፡ ባለው ክርክር ትንሽ ልጅ ነው ብሎ ፡ ሳይንቀኝ በክብር ተሚወያዩበት ፡ አስጠራኝ ተደብር እኔም ተናገርኩኝ ፡ ፍርዱን በዝርዝር ችሎታው የለኝም ፡ አንተን ለመምከር አንተም አትመለስ ፡ ታስበው ነገር አገርክን ወዳጅ ነህ ፡ ጨካኝ ነህ ተምር እንግሊዝ አያውቅም ፡ ይሄንን ሚስጥር እንግሊዞች ላንተ ፡ ያስባሉ ሸር ያበሻ መኳንንት ፡ ለእንግሊዝ ሲያብር ማጥቃት አንኳን ባትችል ፡ የእንግሊዝን ጦር መጨረሻው አንኳን ፡ ነገሩ ባያምር በሚያቀርቡት ሃሳብ ፡ አትደራደር እጅህን እንዳትሰጥ ፡ ህዝቡ እንዳያፍር ጀግንነት ተገምዶ ፡ ባንተ ይቋጠር መቸም ሞት አይቀርም ፡ ስምህን አሰር ጠቅላላ ዙሪያውን ፡ ባበሻ ምድር ላገሩ ሞተላት ፡ ይበልህ አገር ሸሂድ ትሆናለህ ፡ ስትገባ ተቀበር ይሄነን ስነግረው ፡ ፊቱ አለ ቅይር እንደ አንበሳ አገሳ ፡ ሆነ እንደ ነብር ድሮም አይፈልግም ፡ ስሙ እንዲሰበር ቴዎድሮስ ሞት አይፈራም ፡ ይጠላል ነውር ማንንም ሳይፈራ ፡ ፊቱን ሳያዞር በጁ ታሪክ ሰራ ፡ አጃኢብ ታአምር ተዚህ በላይ ደፋር ፡ አለ ወይ ባገር ዩሐንስ አስጠራኝ ፡ አባቴን ሳይቀር መቶ አመት ያለፈው ፡ አዛውንት ነበር መሄድ ስለማይችል ፡ መራመድ በእግር በእንጨት ሰው ወሰደው ፡ ተረዳድቶ አገር ቁረብ ተባለና ፡ መልሱን ሲናገር መስራት ትችላለህ ፡ የሻህን ነገር ይቆርባል ብለህ ግን ፡ እንዳትጠረጥር እኔንም ብትገለኝ ፡ ልጄንም ብታስር ሃይማኖታችንን ፡ እንደማንቀይር ይሄንን ልንገርህ ፡ በግልጽ በዟሂር ብሞት ይሻለኛል ፡ ዛሬን ባላድር ሻሂድ ሁኖ መሞት ፡ ለእስላም ልጅ ነው ክብር ላኢላሃ ኢል ፡ አሏህ ፡ አላሁ አክበር አንድ ተራ ሙስሊም ፡ ይሄን ሲናገር እስላም ይጥፋ ተብሎ ፡ ባበሻ ምድር ዑለማው ቃልቻው ፡ ሲደነጋገር በዛች መጥፎ ሰዓት ፡ በዛች በምትመር ህጉን መቃወም ነው ፡ ንጉሱን መድፈር እንደ ስልጣን የለም ፡ ቆሻሻነ ነገር እስላም ይጥፋ ተብሎ ፡ አዋጅ ሲነገር ጠቅላላ በድፍን ፡ ባበሻ ምድር በዩሐንስ ትእዛዝ ፡ በዘረጋው ሽር ላይሳካ ጉዳይ ፡ አዋጁ ላይሰምር አንድኛው ሊገደል ፡ አንዱ ሲታሰር በእስላም ይስቅ ፡ ነበር ያበሻ ኩፋር ያአላህ ባሪያ ሲሞት ፡ የጀሊል አሽከር ዩሐንስ ኣበዛው ፡ አለፈ ድንበር ለኔና ላባቴ ፡ መግደል ሲሞክር ምንም ሳናጠፋ ፡ ሰው ሳናስቸግር ተይዘን ስንሄድ ፡ ጉድ እያለ አገር በተወለድንበት ፡ ባደግንበት ሰፈር አላህን ለመንነው ፡ አልቅሰን ተምር ለኛ ያሰበው ሞት ፡ ወደሱ እንዲዞር ብዙ ጊዜ ፡ ሳይቆይ ፡ ሳይውል ሳያድር ተመትቶ ወደቀ ፡ በድርቡሽ ብትር ተለይቶ ራሱ ፡ ታንገቱ እስቲበር ተጦር ላይ ተሰክቶ ፡ ራሱ እስቲዞር በደርቡሾች ግዛት ፡ በሱዳን አገር መለየት ይችላል ፡ አላህ ማበጠር የተደባለቀን ፡ ለይቶ ማንጠር የሐንስ የእስላሙን ፡ አንገት ሲቆጥር ስንት እንደገደለ ፡ ስንት እንደሚያስር አላህ ክፈል አለው ፡ የእስላሙን ብድር የሙስሊሞቹ ደም ፡ ፈሶ እንዴት ይቅር በሰፈርካት ቁና ፡ አንተም ተሰፈር ፍርዱ ከባድ ነበር ፡ ጌታችን ቃዲር ተዚህ ላይ ያበቃል ፡ የዩሐንስ ዐምር ምኒሊክ ፈተነኝ ፡ በብዙ ነገር ጠንቋዩን ሰብስቦ ፡ ዘግቶ በአንድ አጥር ሊገደሉ ተብሎ ፡ ህዝቡ ሲሽበር እኔንም አስጠራኝ ፡ ላከብኝ አሽከር እሽ ብየ ሄድኩኝ ፡ ትዛዙን ላከብር አላህ የሻው ነገር ፡ ምን ጊዜም አይቀር ጅን መቶት ተብሎ ፡ ህዝብ ሲነጋገር መልሱን ነገርኳቸው ፡ አድርጌ ዝርዝር ቃሌ ሳይዛነፍ ፡ ሳልደናገር አላሳፈረኝም ፡ ሀሊቁል ጀባር እንግዲያ ሌላማ ፡ ምን አለኝ ቀድር የፈረድኩት ነገር ፡ አንዷም ሳትቀር እየደረሳቸው ፡ ያምኑብኝ ጀመር ስድቡም ቀነሰልኝ ፡ የሰው ቁጥር አላህ ሲያሳምረው ፡ ሰው እጣው ሲወጣ አመት አስቀመጠኝ ፡ ተኸልዋ ሳልወጣ ወዲያው መናብ አየሁ ፡ አንበሳ ሲመጣ ነብር ከኋላየ ፡ ጅብ ከፊቴ መጣ ሁለቱ ሲጣሉ ፡ ጅቡ ደነገጣ ነፍሴን አውጭኝ ብሎ ፡ ሮጦ አመለጣ ግመል የጋለበ ፡ የሆነ ስው መጣ ከዛፍ ስር ሆነና ፡ አስሯት ተቀመጣ ነብሩን እያሻሸ ፡ አንበሳው ላይ ወጣ ይታገለው ጀመር ፡ እየተቀናጣ ይበሉታል ብየ ፡ ልቤ ደነገጣ ነብሩ በረረና ፡ ወደ ሰማይ ወጣ አንበሳው መሬቱን ፡ ጫረና ረገጣ እሱም በሮ ሄደ ፡ ወደ ሰማይ ወጣ ሰውየው ሂድ አለኝ ፡ ለቀቀኝ በነጣ ግመሊቱ ቀረች ፡ ተዛው ተቀምጣ ሰውየው ከወንዙ ፡ ውሃ ቀድቶ ጠጣ ትንሽ ቆየት ብሎ ፡ ከዛፉ ላይ ወጣ ተዛፉ ቀንዘሎች ፡ ትንሽ ቆራረጣ በጁ አፍተለተለው ፡ አንሚጥል ጣጣ እንዷን መዘዘና ፡ ወደኔ እየመጣ ግመሏ ታይ ነበር ፡ ወደ ላይ አንጋጣ እየመጣ ሳለ ፡ አለው እንደማዳጣ ሁሴን ብሎ ጠራኝ ፡ ወደኔ እየሮጣ እኔም ለበይክ እልኩኝ ፡ ሰላምታ ልስጣ ተቀበል እንካ አለኝ ፡ ይሄ ነው ያንተ እጣ ተቀብየ ሳየው ፡ የስጠኝን እጣ ተራስ የሚለበስ ፡ ይመስላል ባርኔጣ በውስጧ ቀይ ናት ፡ ሲያዩዋት ተገልብጣ ሰፋ ትለኛለች ፡ ትንሽ ተለጥጣ ተራሴ አጠለቅኳት ፡ ድምጧ ግን ሲንጣጣ መናቡን አይቸ ፡ ለሰው ሳላወራ በሰባተኛው ቀን ፡ መጣ አንድ ቀብራራ መሰንቆና ዋሽንት ፡ በጁ ይዞ ጭራ ከኔ ጋር አደረ ፡ ጫት ሲቅም ሲያወራ ማሲንቆ እየመታ ፡ ሲዘፍን ሲያቅራራ ዶሴ ተሸክሞ ፡ መጣ አንድ ገታራ እሱም ቁጭ ብሎ ፡ ትንሽ አወራራ እኔም ዝም ብዬ ፡ እያቸው ነበራ ተላይ ድምጽ ሰማሁ ፡ ቁርአን እየቀራ ዙሬ ማየት ጀመርኩ ፡ በቀኝም በግራ ተሩቅ በሮ መጣ ፡ አንድ ነጭ አሞራ ፊቱ ሰው ይመስላል ፡ ክንፉ እንደ ጆቢራ ተትክሻ የላይ ፡ አረፈ ሰፈሩ ተኔ ላይ ቁጭ ብሎ ፡ ሌላ አሞራ ጠራ እሱም ብዙ አልቆየም ፡ መጣ እየበረራ ሽልምልም ያለ ነው ፡ ልክ እንደ ባንዲራ ሁሴን ጅብሪል ብሎ ፡ በስሜ ተጣራ እኔ መሄዴ ነው ፡ ወደ ሌላ ስፍራ ከኔ ጋር ለቀረው ፡ ለዛ ለጆቢራ ብሎ ተናገረው ፡ ሁሴንን አደራ እንዳትለይ ከሱ ፡ በሄደበት ስፍራ መቁረጫ ጎራዴ ፡ መክተፊያ እንደካራ ጫፏ ሹል የሆነች ፡ የብረት ከዘራ በእጄ አስያዘኝና ፡ በሮ ሄደ ዙራ አላህ ሲያመቻቸው ፡ ነገሩ ሲሰላ በስምንተኛው ቀን ፡ ጫት ስንቅም ስንበላ እየተሟሟቀ ፡ ራምሳው ቢስሚላ ከውጭ ሰው መጣ ፡ መልኩ ያለቀላ ብሎ ተናገረ ፡ ሁሴን ቡኑን አፍላ ያስብከው የልብህ ፡ ሃጃህ እንዲሞላ እኔም እየከደምኩ ፡ ቡናውን ሳፈላ ይመርቁኝ ጀመር ፡ ሁሉም በጠቅላላ እኔም አሚን አልኩኝ ፡ ሃጃዬ እንዲሟላ ተመጅሊሱ ገባ ፡ ተውጭ መጥቶ ሌላ እሱም መራረቀኝ ፡ እያለ ማሻአላ ብዙ ሰው ይውደድህ ፡ አንተም ሰው አትጥላ ስምንት ቀን አደርኩ ፡ ሳትናገር አፌ የቤቱን ግድግዳ ፡ ግንዱን ተደግፌ ፊቴን እየታጠብኩ ፡ እንዳይመጣ እንቅልፌ ጩኸት እንዳልሰማ ፡ ጀሮየን ወትፌ የሸሆቸን ኪታብ ፡ በጎኔ ታቅፌ እንዲቀመጡበት ፡ ጋቢዬን አንጥፌ ሱሪዬንም ትንሽ ፡ ወደ ላይ አጥፌ ጭቃ እንዳይነካብኝ ፡ በደንብ ከፍክፌ ብዙ እንደሰራ ሰው ፡ ላቤን አንጠፍጥፌ ጉዝጓዝ ተጎዝጉዞ ፡ አሩቲና ጨፌ አይገርማችሁም ወይ ፡ ሳልደክም ማትረፌ? ፡፡፡፡፡፡፡፡፡ ፡፡፡፡፡፡፡፡፡ ሸሆች ሽማግሌዎች ፡ ትላልቅ አበጋር ስማቸው ገናና ፡ የታወቁ ባገር መናቡን ለነሱ ፡ ነግሬአቸው ነበር መናቡን ፈሰርነው ፡ አንተ ስትናገር ህልም እንደፈቺው ነው ፡ ይባላል በኛ አገር ጠጅ እየቀማመስክ ፡ ጫት ስትቅም ስትኖር ከስልጣን ላይ ያለ ፡ ባልጋም ላይ በወንበር ሁሉም ይፈራሃል ፡ እንዳትጠራጠር ሁሉም እየፈራህ ፡ በዋልክበት እደር ስላንተ ይወራ ፡ ስላንተ ይነገር በቆላም በደጋ ፡ በከተማም ገጠር የረገምከው እርጉም ፡ የመረቅከው ይመር በሄድክበት ይቅናህ ፡ አያጋጥምህ ችግር ጠላት እንዳይነካህ ፡ ጎራዴ እንካ በትር ሃሲድ የምትመታ ፡ ትላልቅ ሹም ሳይቀር ጀባ ብለንሃል ፡ እነሆ በዟሂር አሚን ማለት ብቻ ፡ ሆነ የኔ ነገር እየገባኝ መጣ ፡ ነገሩ ቆየ እንጅ አንድ ነገር ሲቆይ ፡ አየ ሲያሰለች አላህ ታደረገኝ ፡ ለክልቁ ወዳጅ ጫቴን እየቃቃምኩ ፡ እየጠባሁ ጠጅ ማሲንቆ እየመታሁ ፡ ልወዛወዝ እንጅ በጭራ በዋሽንት ፡ ሰው ባልነካው በጅ ለሁሉ እንዲጠቅም ፡ ዱዓው እንዲበጅ ዱአችን ይሰማ ፡ ከጌታችን ደጅ ሁል ጊዜም ለማኝ ነው ፡ የዱዓ ነጋጅ የኸይር ዛፍ ሲተክል ፡ ይውላል ሲያበጅ ፍሬው አይቀንስም ፡ ይጨምራል እንጅ ስጦታው ይገርማል ፡ ሃሊቁ ረህማን አናወራዋለን ፡ ምን አስደበቀን ግልጥ እንዲሆንለት ፡ ብለን ነው ህዝቡን ስንት መጥፎ ነገር ፡ አላህ አሳየን በጣም የሚያስጠላ ፡ የሚዘገንን ምን እንሆን ነበር ፡ ያን ቢያሸክመን የሰጠኝን ይዤ ፡ ልበል ተመስገን ያልጣመው ይሳደብ ፡ ያመነም ይመን ጥቁር ጭራ ፡ ይዘን ድቢ እየመታን ሃሲድ እንዳይነካን ፡ አውሊያ እየጠራን አምስት ወቅት ሶላት ፡ እየሰጋገድን ማር ተበጥብጦልን ፡ ጠጅ እየጠጣን ሰው ያልነካው እጣ ፡ ጀሊሉ ሰጠን መጭውን አየነው ፡ ጉድ አጃኢቡን ለሰው ይመስለዋል ፡ ያወራሁ ውሸት አያደናገርኩት ፡ እያታለልኩት የግጥም አድርጌ ፡ ፍርድ ስፈርድለት አዳምጠኝ ልንገርህ ፡ ሚስጥሩን በእውነት አለም ስትስቅብኝ ፡ እኔም ሳቅኩባት ታለፉች በስተቀር ፡ ያለን በሂወት ሳለፉ ሳልደክም ፡ ምንም ሳልታክት ተከትቦ አየዋለሁ ፡ ስሙን ወደፊት በወርቅማ ቀለም ፡ በነጭ ወረቀት ይሄ ስጦታ ነው ፡ ታላህ ራህመት ገና ሳይፈጠር ፡ ሳይኖር በሂወት ስሙን ይነግረኛል ፡ ማን እንደሚሉት ታዲያ ሰው አይገባው ፡ ይሄን ሲነግሩት እንዲያው ዝም ብየ ፡ ማወራ መስሎት ዝምበል ሲሉኝ ነው ፡ የምወሻክት ምን አስለፈለፈኝ ፡ ሊታይ ወደፊት እንደዚህ ነው ፍርዱ ፡ መሆን ያለበት ባይኔማ ከታየኝ ፡ ቁጭ ብሎ ተፊት እያየሁት አይደል ፡ ምኑን ፈረድኩት ስር ሲምስ የሚያድረው ፡ ጠንቋይ በሌሊት ወዶ መሰለህ ወይ ፡ ነው እንጅ ጨንቆት ሰዎች እንዳያዩት ፡ እንዳይነቁበት ስንት ሰው ጠይቆ ፡ ስንት ሰው ነግሮት ያውም ካጋጠመው ፡ ከተሳካለት ለውን አሳምኖ ፡ ገንዘብ ለማግኘት ሳወራህ አዳምጠኝ ፡ እንዳትታክት አውሰልስለውና ፡ እስኪ እሰብበት በኔና በነሱ ፡ ያለው ልየነት ብዙ አያስቸግርም ፡ ይሄን መገመት ከቤቴም ቁጭ ብየ ፡ መንገድም ብወጣ ምግብ እየበላሁ ፡ ወይ ቡና ስጠጣ ወይ ሱብሂ ሰግጄ ፡ ገና ጣይ ሳይወጣ ደስ ብሎኝ ብቀመጥ ፡ ከፍቶኝም ብቆጣ ሲጋፋ አየዋለሁ ፡ መሿለኪያ ሲያጣ ተልባ እንደተቆላ ፡ ከፊቴ ሲንጣጣ ስሙን ይነግረኛል ፡ ዋሪዳው ሲመጣ ምንድን እንደሚሆን ፡ የዛ የሰው እጣ ገና ሳይወለድ ፡ ከዱንያ ሳይመጣ የሚያገኝም ቢሆን ፡ ወይንም የሚያጣ ሰካራምም ቢሆን ፡ መጠጥ የሚጠጣ ስልጣንም አግኝቶ ፡ ከወንበር ቢወጣ ተይዞም ቢታሰር ፡ ተገሎም ቢቀጣ በቅሎ እንኳን ብትጥለው ፡ ሩጣ ፈርጥ ጣ አላህ ይነግረኛል ፡ ይሄ ነው የኔ እጣ እውነት ትውጣለች ፡ ውሸትን ገልብጣ ተከምራ አትቀርም ፡ ተጋግራ እንደ ቂጣ እውነት ከውሸት ቤት ፡ አትገባም ተሽጣ ተዚህ በላይ እኔ ፡ ምን ላውራ ፡ ምን ላምጣ አምሳ ዓመት ስናገር ፡ ሰምተው ጉድ እያሉ ሰምተው እንዳልሰሙ ፡ አላየንም አሉ ያላወቁ መስለው ፡ ሰው እያጃጃሉ እንደ ፍልፈል አፈር ፡ ሰው ሲፈላፈሉ ዝም ብለው ተነስተው ፡ የሚቀኑም አሉ መደበቅ መታገስ ፡ መያዝ የማይችሉ እኛም ሰደድናቸው ፡ አፍረው እንዲተሉ ነገሩን ሳያውቁት ፡ እንዲንቀዋለሉ ቀሪው እንዲፈራኝ ፡ ውሸት እንዳይሉ ኋላ እንዲገባቸው ፡ አድረው እየዋሉ ተአላህ እንደሆነ ፡ ስጦታው በሙሉ ጥቅም እንደሌለው ፡ ሁሉም በጥቅሉ ህዝቡ እየሰማቸው ፡ ሃበሻ በሙሉ ልክነው አምነናል ፡ ቶበትን እስተሚሉ አርፈው ይቀመጡ ፡ ሰው ተሚያታልሉ አላህ አይወደውም ፡ በዚህ ተቀጠሉ መታረቅ ይሻላል ፡ መሸመጋገሉ ብዙዎች በቅናት ፡ ነደው ተቃጠሉ =============================== *** *** *** *** *** =============================== 50 ዓመት ኸደመኝ ፡ ሙሀመድ ኑር ኢሳ መድና ወረቀት ፡ ተጁ ሳያነሳ ይከትበው ነበረ ፡ ዋሪዳው ሲነሳ ተጠንቅቆ ነበር ፡ ቃሌ እንዳይረሳ ደከመኝም ሳይል ፡ ለወቅቱም ሳይሳሳ እኔ እንደ ሸህ ሁኘ ፡ እሱ እንደ ደረሳ የዚህ ሰው ውለታ ፡ መቸም አይረሳ ኋላ ታማሚ ሆንኩ ፡ ሰውነቴም ከሳ ያዝንልኝ ነበረ ፡ እንዳልሞት ሲሳሳ ምግብ አያስበላኝ ፡ ጨጓራው ሲነሳ እንገናኝ ነበር ፡ ወይ በራት በምሳ አይዞህ ብላበት ፡ ይለኛል ቅመሳ ለጀነት ይበለው ፡ ታአላህ ያግኝ ካሳ ሁላችን ሟቾች ነን ፡ አጀላችን ደርሳ ታሪክ ግን ይቆያል ፡ ተሎም አይረሳ ሰው ታላበላሸው ፡ ሃሲድ ታልተነሳ ቃልቾቹም ጠሉኝ ፡ ጠጅ ይጠጣል ብለው ደብተሮችም ጠሉኝ ፡ ሹም ተጠጋ ብለው ባለዛሩም ጠላኝ ፡ ሰው ሄደለት ብለው ፉቅራውም ተጠጋኝ ፡ ምን ይፈርዳል ብለው ሰምቸ እንዳልሰማሁ ፡ ዝምብዬ መኖር ነው ሰውን አውቀዋለሁ ፡ ያበሻ ልምድ ነው ቃልቻ ነኝ ብትል ፡ ወየት ተምሮ ነው፧ ወልይ ነኝ ብትል ፡ ዘሩ ተነማን ነው፧ ጠንቋይ ነኝ እንዳትል ፡ ሁሉም ሰው ጠንቋይ ነው እኔ የምኖረው ፡ እኒህን ችየነው ባለዛሩም አያውቅ ፡ ፉቅራውም ፉቅራ ነው ባላገሩም አያውቅ ፡ እንደኔ ጃሂል ነው እኔን ቅር የሚለኝ ፡ በቃልቾቹ ነው አላህ እንደሚሰጥ ፡ ለሚፈልገው ሰው አያጠራጥርም ፡ ጥያቄም አይኖረው ስጥ አት ስጥ ብሎ ፡ ሰው ለአላህ አያዘው ቃልቾች ያውቃሉ ፡ ይሄንን ደህና አርገው የሚከራከሩኝ ፡ ታዲያ ለምንድን ነው? እኔ ተሰው በላይ ፡ ምንድን አውቄ ነው? ወይንስ ተመጽሐፍ ላይ ፡ ገልጨ አንብቤው ነው? የሄነን ሁሉ ፍርድ ፡ የምለፈልፈው አላህ ላልተማረ ፡ ለእንደኔ አይነቱ ስው አላህ ተሙእጅዛው ፡ ጌታችን ቢሰጠው አገረ ገዥ ቢሆን ፡ ስልጣን ቢያስጨብጠው ሃፍታሙን ደሃ አርጎ ፡ ደሃውን ቢያከብረው ታማሚ ስው ቢድን ፡ በሽታው ቢለቀው አላህ ይሄን ማድረግ ፡ አይችልም ልንል ነው? ይሄን ሁሉ ፍጥረት ፡ አላህ የፈጠረው የቱን ሰው ጠይቆ ፡ ማንን አማክሮ ነው? እናንተን አማክሮ ፡ ፈቅዳች ሁለት ነው? የግሉ የሆነ ፡ አላህ ስልጣን አለው ሰው የማይደርስበት ፡ ማነም የማያውቀው እኔንም የሰጠኝ ፡ እውቀቱን እሱ ነው እናንተ ለፍልፉ ፡ አውነቱ ይሄ ነው አንዳንዴስ ይገርማል ፡ እውነታቸውን ነው እንደነሱ ሁኘ ፡ እራሴም ባስበው በጣም ያስቸግራል ፡ ነገሩ ከባድ ነው አሁንም መልሶ ፡ ዙሮዙሮ ያው ነው ግን በመጀመሪያ ፡ አላህን ማመን ነው ምንም ነገር አይሆን ፡ እሱ ሁን ካላለው ቀን ብንደክምበት ፡ ሌት ብንታገለው ነገሩም ባይጥመን ፡ ባንወደው ብንጠላው ስንዝር አትጨምርም ፡ ያው እጣህ እጣህ ነው ተዚህ በተረፈ ፡ ለናንተ ልተወው =========================== *** *** *** *** *** =========================== ዙሪያውን መጡብኝ ፡ በግራም በቀኝ እኔ ምን አቅም አለኝ ፡ አላህ ይሁነኝ በነ ቄስ ወርቅነህ ፡ በነ መምህር ግርማ በአለቃ ውብነህ ፡ ነስር ባላገኝ በአለቃ ቀለምወርቅ ፡ በነ ይመር አደም ነስር ባላገኝ በአለቃ እዮብና ፡ በአውገረድ አለምነሽ ነስር ባላገኝ እንዴት እሆን ነበር ፡ እስቲ ንገሩኝ? እኝህ ተዋርደው ነው ፡ ንጉስ የፈራኝ ይሄ ባይሆን ኑሮ ፡ አላህ ባይረዳኝ ይኖሩ ነበረ ፡ እንዳዋረዱኝ ከክርስቲያኑ እስላም ፡ ነው የጠመመኝ ሰው ችላ ስትለው ፡ ያደርግሃል ሞኝ ባይኔ እያየኋቸው ፡ የሚያታልሉኝ እንዴት ቢንቁኝ ነው ፡ እንዴት ቢደፍሩኝ? ስድቡ አልበቃ ብሎ ፡ የሚያዋርዱኝ በመውሊድ በለቅሶ ፡ ላይ ስንገናኝ ጠጅ ይጠጣል ብለው ፡ ስሜን ሲያጠፉኝ እኔም ወድጀ አይደል ፡ አላህ ጥሎብኝ እኔም ባልጠጣሁት ፡ እንዴት ደስ ባለኝ ሰው ተማወናጅል ፡ ለኔም በረዳኝ ግን አላህ ታዘዘ ፡ ተፈረደብኝ እኔ ምንድን ላድርግ ፡ ሰዎች ምከሩኝ ወይንም እንዳልጠጣው ፡ ዱአ አድርጉልኝ እንዳልነካው በጄ ፡ ደግሞ እንዳያምረኝ ጠጥቼ አያሰክረኝ ፡ ወይ አያሸናኝ የት እንደሚገባ ፡ እኔም አይገባኝ ሰውን ቢያስገርመው ፡ ምንም አይገርመኝ መጅሊስ ላይ ስቀመጥ ፡ ነው ትዝ የሚለኝ ደግሞ ሌላው ነገር ፡ የሚያስገርመኝ በሮመዳን ወራት ፡ ትዝም አይለኝ ይሄን ስነግራችሁ ፡ መቸም አታምኑኝ እንለፍላፊ ሰው ፡ ነው የምታዩኝ ያትክልቱን ቦታ ፡ ሚኒሊክ ሰጥቶኝ ድህነቴን አውቆ ፡ ሃፍት እንደሌለለኝ አቶ ደጃች ሊበን ፡ ወሰደው ቀማኝ ፍርድህንም አቁም ፡ ብሎ ላከብኝ የምፈራው መስሎት ፡ የምለው ሙጥኝ እንዳልናገር ነው ፡ ሰው እንዳይሰማኝ ስተቱን ስለሚያውቅ ፡ እንደ በደለኝ ሌት ቀን ፡ በዛች መሬት ፡ ሲጨቀጭቀኝ ለቅሶዬን ፈጣሪ ፡ ጌታዬ ሰማኝ መሬቱን አገኘ ፡ እንደጠየቀኝ እሱም ስላረፈ ፡ እኔም አረፍኩኝ ነግሬያችሁ ነበር ፡ ፊት ሳልታመም ሁሉም እንደሚሆን ፡ ያየሁት በህልም ጠጅ እንደምጠጣ ፡ ጫት እንደ ምቅም ለፍልፌ ነበረ ፡ ያመነኝ የለም በዚህ የሚስማማ ፡ አይኖርም እስላም ለቃልቾቹማ ፡ ከባድ ነው ፡ ሸክም እንኳን ጠጅ ጠጥቼ ፡ ክልክሉን ሃራም ማውራት ይወዳሉ ፡ ወሬ መቀመም ጠጅ መጠጣቱ ፡ ክልክል ነው ሃራም በቁርዓን በሐዲስ ፡ በዲነል ኢስላም አላህ ታዘዘብህ ፡ ሰው መተው አይችልም ይችላል ይበለን ፡ ይንገረን አሊም ብልሃቱን ይንገረን ፡ መላ ይጠቁም ለሱም ሰዋብ አለው ፡ ለኛም አለው ፡ ጥቅም እሱ ተሻብህ ግን ፡ አዚዙል ከሪም እንደ በሽታ እየው ፡ እንደ መታመም ከተለከፈ ሰው ፡ በሽታ ህመም ለመዳን ይጥራል ፡ በዶክተር በሃኪም መድሃኒት ይወስዳል ፡ በመደጋገም ሊድን ይፈልጋል ፡ ተዛ መጥፎ ህመም መዳን የማይፈልግ ፡ ንገሩኝ በስም እኔ እርግጠኛ ነኝ ፡ አንድ አይገኝም እኔም ልዳንና ፡ ልኑር በሰላም አላህ በጥበቡ ፡ አላህ በራህመቱ ገና ሲወጥነኝ ፡ ሲፈጥረኝ ተጧቱ አለኝ ክፉ ዱዓ ፡ የማይበርድ ስለቱ ጎራ የማይከልለው ፡ ወንዝና ጅረቱ ከፈለኩት ቦታ ፡ ሄደው የሚመቱ በሩቅም በቅርብም ፡ የማይሳሳቱ ሰዎች ይጠሉኛል ፡ እንዲሁ በከንቱ ይከራከሩኛል ፡ እየተሟገቱ ቀናተኞች ናቸው ፡ ለወሬ አይታክቱ በጣም ይገርመኛል ፡ የአላህ ቸርነቱ ይሄን አይነት እጣ ፡ ለኔ መሰጠቱ ይቀሙኝ ነበረ ፡ ቢቻል መቀማቱ ዝም ብሎ ፡ ያውራ እንጂ ፡ ሁሉም በየቤቱ አላህ ስለሰጠኝ ፡ ማን ወንዱ ነክቷቱ ትክክለኛው መልስ ፡ ይሄ ነው እውነቱ አዱኛ ደህና ሁኝ ፡ እኔ ጋለብኩሽ ምስክሬ አንች ነሽ ፡ አዋጅ እንዳትረሽ በሃቅ መስክሪ ፡ እንዴኔ እንዳትዋሽ የሚያውቀኝ ብዙ ነው ፡ እንዳትወቀሽ ብርሃንሽ ሳይጠፋ ፡ ለኛ አጨልመሽ እኔን በታች አርገሽ ፡ በላይ ታረገሽ ሰው ትመገቢያለሽ ፡ ግን አያጠግብሽ በቃኝ የማትይ ፡ የማይጠግብ ሆድሽ ማንስ ሃይል ኖሮት ፡ አንችን ሊገፋሽ ቢሸሸግ ቢደበቅ ፡ የማያመልጥሽ እኛም ልንወድቅ ፡ እሷም ላትሸሽ ስሟን ብጠይቃት ፡ አለችኝ ወራሽ ስሜን ብትጠይቀኝ ፡ አልኳት ፡ ነኝ ብላሽ ኃላ እንዲህ ልትሰድበኝ ፡ ልትለኝ በስባሽ ጨካኝ እዝነት የላት ፡ ለትልቅ ትንሽ አንች ሰው አትረሽም ፡ ሰውም ቢረሳሽ ጊዜሽን ጠብቀሽ ፡ ብቅ ትያለሽ በዘጠና ስምንት ፡ ገላችን ፈራሽ ውሳኔው ተላይ ነው ፡ ተጌታ ተአርሽ አንችም ተልከሽ ነው ፡ አይደለም ወደሽ የሁሉም ፈጣሪ ፡ አላህ ነው አዞሽ ሂጅና አምጭው ተብለሽ ፡ ሁሴንን ይዘሽ ተዘጋጅቻለሁ ፡ እየጠበኩሽ እንቺ ተረከቢኝ ፡ ነፍሴን ለሱ አድርሽ የሰው ሃብት ፡ የሰው ነው ፡ ይሄን ታውቂያለሽ ምን አስለፈለፈኝ ፡ ላንች ምን ጠፍቶሽ የመጨረሻ ቃል ፡ ይሄን ልንገርሽ። *** *** *** *** *** *** *** *** ***